ሚያዚያ 13/ 2013 (ዋልታ) – የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ለማስቀጠል የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሼኬዲ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የቢሮ ስብሰባ እንዲጠሩ መጠየቅ እንደሚገባ ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የተጻፈው ደብዳቤ ያትታል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሚያዚያ 13 ቀን 2021 ለጻፉት ደብዳቤ በሰጡት ምላሽ የድርድሩን ሂደት እንዳልተሳካ መቁጠር ተገቢነት አንደሌለው ገልጸው፣ ለዚህም የመርሆዎች ስምምነት መፈረም፣ የብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንስ ምርምር ቡድን (NISRG) መቋቋሙና የግድቡ ውሃ አሞላል መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችን በሂደቱ ለተመዘገቡ ስኬቶች በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል ብለዋል።
የኪንሻሳውን ስብሰባ የሚጠቅሰው ደበዳቤው፣ ሲራዘም የቆየውና በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንደገና መጀመር፣ የድርድሩ ታዛቢዎች የሆኑት የአውሮፓ ሕብረት፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ በድረድሩ የሚኖራቸው ሚና እንዲጠናከር መደረጉ እንዲሁም የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር የማስተባባር ተግባራቸውን ለመወጣት አንዲችሉ አስፈላጊ ሀብቶችን በሙሉ መጠቀም አንደሚገባቸው በስብሰባው መግባባት ላይ መደረሱን ደብዳቤው አስታውሷል።
ደብዳቤው በሁሉም ተዳራዳሪዎች ተቀባይነት ያለው ውጤት ላይ ለመድረስ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ህጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሷል።
ምንም እንኳ የሶስትዮሽ ድርድሩ ለዘጠኝ ጊዜያት መስተጓጎል የገጠመው ቢሆንም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንዲካሄድ የአፍሪካ ህብረት ላመቻቸው እድል አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የድርድሩ ተሳታፊ አካላት በቅን ልቦና የሚደራደሩ ከሆነ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል በመግለጽ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎትት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡: