ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ እና በሉዓላዊነቷ ላይ ለሚሰነዘሩባት ድፍረት አዘል ጫናዎች እንደማትንበረከክ ምክትል ጠቅላይ ሚነስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
“እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት፥ በመከባበር እና በአሸናፊነት መርሆዎች በዓለም አቀፍ አውድ በነፃነት እና በተወዳዳሪነት ፀንተን እንቀጥላለን” ብለዋል አቶ ደመቀ 58ኛውን የአፍሪካ ቀን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የመላው አፍሪካውያን የአንድነት ጥላ ምልክት ለሆነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ህብረት) 58ኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ።
ከድርጅቱ ምስረታ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ቀን በየዓመቱ ሲዘከር ሃገራችን ኢትዮጵያ ነፃነቷን እና ክብሯን በቀዳሚነት አስጠብቃ መዝለቋ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ደማቅ ታሪካዊ ትርጉም ይቸራል።
ከ125 ዓመታት በፊት በወራሪ ሃይል ሃገራችንን በቅኝ የማሳደር ቀቢፀ ተስፋን ተከትሎ፤ የቁርጥ ቀን ጀግኖቻችን ባደረጉት አኩሪ ተጋድሎ የአድዋ ድል ባለቤት የመሆን ዘለዓለማዊ ዕድል ተጎናፅፈናል።
በተለይ ሚያዝያ 27 ቀን 80ኛ ዓመት የድል በዓል ያከበርንበት ታሪካዊ አውድ፤ የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ከፍታ የተገለጠበት ተጨማሪ የድል አድራጊት እሴት አውርሶናል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ቀንን የምናከብርበት ታሪካዊ ምክንያት እንደ አህጉር በፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ የተመዘገበ አኩሪ ድል ለመዘከር ሲሆን፤ መቼም ቢሆን በውጭ ኃይሎች ጫና የማንበረከክ ስለመሆናችን ህልው ማረጋገጫ ነው።
በዚህ ወቅት በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ እያማተሩ በሉዓላዊነታችን ላይ ለሚሰነዘሩብን ድፍረት አዘል ጫናዎች እንደማንንበረከክ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል።
በዚህ አግባብ እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት፥ በመከባበር እና በአሸናፊነት መርሆዎች በዓለም አቀፍ አውድ በነፃነት እና በተወዳዳሪነት ፀንተን እንቀጥላለን።
በመጨረሻም የድል አድራጊነት ወኔያችንን በማጥበቅ ኢትዮጵያ በመጪው ጊዜያት ለመላው አፍሪካ የነፃነት እና የኩራት ቀንዲል ሆና እንድትዘልቅ በጋራ እንድንረባረብ አደራ ለማለት እወዳለሁ።
መልካም የአፍሪካ ቀን!