የቱሉ ጉዶ ሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ የውሃ መጠጥ ፕሮጀክት ተመረቀ

ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – በቀን 68 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መስጠት የሚያስችል የቱሉ ጉዶ ሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ የውሃ መጠጥ ፕሮጀክት ተመርቋል።

ከቱሉ ጉዶ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች 22 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማምረት የሚችሉ የውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ በአጠቃላይ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጭ መደረጉም ተገልጿል፡፡

በምረቃ መርኃግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም 1 ሺህ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደቻለ ገልጸው፣ ፕሮጀክቶቹ በጥራትና በክትትል የተፈፀሙ ናቸው ብለዋል።

እስከ ሰኔ ባለው ጊዜም እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ለማድረስ እንደሚሰራ ተናግረው፣ ከከርሰ ምድር ውሃ በተጨማሪ የገፀ ምድር ውሃ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የአቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማዎችን ጨምሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የተገነባበት በቱሉ ጉዶ አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በቱሉ ጎዶ የተመረቀው የንፁህ መጠጥ ውሃ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለ900 ሺህ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣልም ነው ያሉት።

በምረቃ መርኃግብሩ በግንባታው አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋራጮች እና ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

(በሱራፌል መንግስቴ)