ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውን የኮቪድ-19 ህክምና ምርምር ተቀላቀለች

ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውን የኮቪድ 19 ህክምና ምርምር ተቀላቀለች።

የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎችን በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አለምሰገድ አብዲሳ እንደገለጹት፤ የህክምና ሙከራ ምርምሩ ለሌላ ህክምና ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ መድኃኒቶች ለኮቪድ-19 ህክምና ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የሚፈተሽበት ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን የሚያግዝ የትብብር መድረክ በማዘጋጀት የኮቪድ-19 ህክምና ክትባትና ምርመራ ዘዴዎችን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ትብብር ከ30 በላይ አገሮችና 500 ሆስፒታሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያም በአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት አማካኝነት በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውን የኮቪድ-19 ህክምና ምርምር በመቀላቀል በአፍሪካ ከግብጽና ደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሶስተኛዋ አገር መሆኗን ኢዜአ ዘግቧል።