የኮቪድ 19 ክትባት ክፍፍል ፍትሀዊ አለመሆኑ ተገለጸ

በሀብት የበለፀጉ ሀገራት የኮቪድ 19 ክትባቶችን በማከማቸት ታዳጊውን ዓለም ወደ ኋላ በመተው ላይ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የክትባቶች ህብረት አስታወቀ፡፡

በሀብት የበለፀጉት ሀገራት ህዝቦቻቸውን በሶስት እጥፍ ለመከተብ የሚያስችል በቂ የኮቪድ 19 ክትባት መግዛታቸውንና ታዳጊ ሀገራት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ዓለም አቀፉ የክትባት ክትትል ቡድን አስታውቋል፡፡

በዚህም ምክንያት በ67 ታዳጊ ሀገራት ውስጥ ከሚኖሩ 10 ሰዎች መካከል ቢያንስ አንዱ ብቻ ክትባቱን በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ያገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ታዳጊ ሀገራት አሁንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለማስቆም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ኋላ መቅረታቸውንም መረጃው ጠቁሟል፡፡

ከዓለም ህዝብ ቁጥር 14 በመቶውን ብቻ የሚይዙ ያደጉት ሀገራት ተስፋ ሰጭ ክትባቶችን ከግማሽ በላይ ለመግዛት ቀድመው ማዘዛቸውም ተገልጿል፡፡

ቡድኑ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ቴክኖሎጂአቸውንና አዕምሯዊ ንብረታቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት እንዲያካፍሉ ያሳሰበ ሲሆን መንግስታትም ከአደገኛው የኮቪድ-19 ተፅዕኖ ለመላቀቅ ክትባቶችን ወደ ታዳጊ ሀገራት ለመላክ ቁርጠኛ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማንኛው ሰው ኪሱ ውስጥ ባለው ገንዘብና በሚኖርት ሀገር ምክንያት ብቻ ህይወት አድን የሆነውን የኮቪድ ክትባት ማጣት የለበትም ሲሉም ክትባቱ ለህዝብ እንዲደርስ ከሚሰሩ የበጎ አድራት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኦክስፋም የጤና ፖሊሲ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለው አካሄድ ካልተቀየረ  በቢሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ደህንነቱ የተረጋገጠ የኮቪድ ክትባትን ለማግኘት ከባድ ይሆንባቸዋልም ተብሏል፡፡

ካናዳ የዜጎቿን ሶስት እጥፍ ለመከተብ የሚያስችል ክትባት የገዛች ሲሆን ከ50 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ  ለ88 ከመቶው ህዝቧየሚሆን በቂ ክትባት መግዛት ችላለች፡፡

ማረጋገጫ ከተሰጣቸው ክትባቶች 96 በመቶ በአደጉት ሀገራት መያዛቸውን የገለጸው ቡድኑ በዚህ ምክንያት 67 ሀገራት የኮቪድን ክትባት የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን ማስታወቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

በትዕግስት ዘላለም