ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ በነፃነት ፀንታ ትቆያለች – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ


መጋቢት 30/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ስላሏት በነፃነት ፀንታ ትኖራለች ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በትምህርትና ስልጠና ዋና መመርያ ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ያሰለጠናቸውን ዕጩ መኮንኖች በሁርሶ የኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ አስመርቋል።

በዚህም በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ስላሏት በነፃነት ፀንታ ትኖራለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያን የማበልፀግና የማፅናት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ጀግኖች ስላሏት ሁሌም በነፃነትና በጀግንነት ትታያለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተመራቂ መኮንኖችም የኢትዮጵያን አይበገሬነት የማፅናትና የማስቀጠል ኃላፊነትን የገቡትን ቃል በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ለምንም ነገር የማትቆሙ፣ ፈተና የሚያበረታችሁ እንጂ ሽብርክ የማትሉ አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ የምታሻግሩ ናችሁ” ሲሉ ነው ተመራቂ መኮንኖቹን የገለጿቸው።

ታሪክ፣ ሃብት፣ ጀግንነትና በሁሉም መስፈርት የሚያኮራ አገር ጠባቂዎች ስለሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል።

ተመራቂ መኮንኖች ውጊያን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ለምርቃት የሚያበቃ ዝግጅትና ታላቅነትን በተግባር ያሳየንበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት “ጉባ” የሚለውን ስያሜን የያዛችሁ በመሆኑ ምርቃቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምረቃዎች ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ተመራቂ መኮንኖችም እራስን በእውቀት በማጎልበት፣ በመትጋት በመማር፣ ዘመናዊነትን በመላበስ ለተሻለ ተግባር ራሳቸውን ለማዘጋጀት እንዲተጉ ማሰሳባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡