ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ አላለፈም

ነሐሴ 18/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴካፋ ዞን የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ ማለፍ አልቻለም።

ሁለተኛው የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ በሞሮኮ አስተናጋጅነት በጥር ወር 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) በመወከል በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በታንዛንያ ከነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም እየተካሄደ የሚገኘው የክለቦች የማጣሪያ ውድድር ዛሬ 11ኛ ቀኑን ይዟል።

በማጣሪያው ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ በአዛም ኮምፕሌክስ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ከኡጋንዳው ሺ ኮርፖሬትስ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 1 ተሸንፏል።

አኒታ ናማታ እና ፊዮና ናቡምባ ለኡጋንዳው ክለብ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ሎዛ ለንግድ ባንክ ብቸኛውን ግብ አስቆጥራለች።

ውጤቱን ተከትሎ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅዳሜ ነሐሴ 21 2014 ዓ.ም የደረጃ ጨዋታ ያደርጋል።

የፊት መስመር ተጫዋቿ ሎዛ አበራ በውድድሩ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች መጠን ወደ 10 ከፍ በማድረግ የማጣሪያውን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራች ነው።

የኡጋንዳው ሺ ኮርፖሬትስ የፍጻሜ ጨዋታውን ከታንዛንያው ሲምባ ኩዊንስና ከርዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ አሸናፊ ጋር ያደርጋል።

ሁለቱ ክለቦች የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰአት በአዛም ኮምፕሌኬስ ያደርጋሉ ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን ውድድሩ አሸናፊ ሴካፋን ወክሎ በአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።