የኢትዮጵያን ባህር ኃይል ለማዘመን ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

ነሐሴ 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን ባህር ኃይል ለማዘመን ከሀገር ውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚሠጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በአዲስ መልክ ከተመሠረተ ጀምሮ የተለያዩ አቅም ፈጣሪ ስልጠናዎችን ከሀገር ውጭ እና በሀገር ውስጥ አባላቱን በማሠልጠን ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ በብላቴ የኮማንዶ እና የአየር ወለድ ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከል ተገኝተው የማሪን ኮማንዶ የሚሠለጥኑ የባህር ኃይል አባላትን ጎብኝተዋል።

ዋና አዛዡ የስልጠና ሂደቱን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ የማሪን ኮማንዶ ሠልጣኞች በማሠልጠኛ ማዕከሉ የሚሠጡ ስልጠናዎችን በድሲፒሊን፣ በሞራል እና በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እየተሠጠ ያለው ስልጠና ከሌሎች የሠራዊት ክፍሎች ጋር በመሆኑ የተሞክሮ እና የልምድ ልውጥ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ያገኛችሁትን ዕውቀት ለሎች ለማካፈል ተግታችሁ ልትሠለጥኑ ይገባል ብለዋል።

ዋና አዛዡ በስልጠና ላይ የሚገኙ የማሪን ኮማንዶ ሰልጣኞች ቀጣይ ለምንሠጣቸው ስልጠናዎች አቅም ፈጣሪ በመሆናችሁ ከማሰልጠኛው የምታገኙትን ዕውቀት አቅባችሁ ባህር ኃይልን ለማዘመን በምንሠራው ሥራ ላይ የድርሻችሁን እንድትወጡ ከወዲሁ ልትዘጋጁ ይገባልም ነው ያሉት።

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮ/ል ቦጃ አጋ በበኩላቸው የባህር ኃይል ማሪን ኮማንዶ ሰልጣኞች በድሲፕሊንም ይሁን በማንኛውም እንቅስቃሴ አርዓያ እንደሆኑ ማንሳታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW