ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በቀጣይ በሚኖራቸው ትብብር ዙሪያ ምክክር አካሄዱ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በቀጣይ በሚኖራቸው ትብብር ዙሪያ ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር ውይይት አካሂደዋል።

ውይይቱን ያካሄዱት በአውሮፓውያኑ ከ2ዐ21 እስከ 2ዐ27 ድረስ ስለሚኖራቸው ትብብር በተመለከተ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ መሆኑ ተመላክቷል።

በውይይቱ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የተለያዩ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ እና የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ናቸው።

ውይይቱም ያተኮረው የኢትዮጵያን የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ እና የአውሮፓ ህብረት የልማት ፖሊሲን በረቂቅ ሰነዱ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ላይ ነው ተብሏል።

የምክክር መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ፣ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የረጅም ጊዜ ጠንካራና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ትብብር ያላቸው መሆናቸውን በማስታወስ እስከ አሁን ህብረቱ ለሚያደረገው ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይም በጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በምርጫ ድጋፍ፣ በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና በግብርና መስክ ህብረቱ ባደረገው ድጋፍ በርካታ አመርቂ ውጤቶች እንደተገኙ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በድህረ ኮቶኑ ስምምነት መሰረት ከህብረቱ የተለያዩ የልማት ድጋፎች ከሚያገኙ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገሮች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ የመልካም ግንኙነት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተነሱት ሀሳቦች በረቂቅ የትብብር ሰነዱ ላይ ተካተው በአውሮፓውያኑ ከግንቦት 2ዐ21 በፊት ለማጠናቀቅ ስምምነት ላይ መደረሱን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።