“ኢትዮጵያ ከ25 ቢሊየን ችግኝ በላይ ናት” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ነሐሴ 8/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ከ25 ቢሊየን ችግኝ በላይ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራችንን ደግመን ደጋግመን በአረንጓዴ ማልበስ ይኖርብናል በማለት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በድሬደዋ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርኃ ግብር ላይ ነው።

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት በ 4 ዓመት ዝናባማ ወቅቶች 20 ቢሊየን ችግኞች መትከልን ግቡ አድርጎ የተነሳ ቢሆንም እስካሁን 25 ቢሊየን ችግኞችን በአራት ተከታታይ አመታት በመትከል ከተያዘው እቅድ የላቀ አፈፃፀም ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ችግኝ መትከል ላይ የተመሰረተ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እያበለፀገች ነው በመሆኑም ኢትዮጵያዊን ችግኝ መትከልን ባህል ማድረግ አለባቸው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልፀዋል።

አክለውም ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን የተፈጥሮ ሀብት አሟጠው የሚጠቀሙ ሳይሆን፤ መቆየት የሚገባውን ጠብቀውና ተንከባክበው ለትውልድ የሚያቆዩ ናቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ በዓመቱ የተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ፤ እንዲሁም በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የተስተጓጎለውን የምግብ ዋስትና ቀውስ ተቋቁማ ማደግ መቻሏ፤ ላለፉት 4 ዓመታት የተሰሩት የተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋፅኦ እንዳላቸው መመልከት ይቻላል፡፡

ደረሰ አማረ (ከድሬደዋ)