ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለጤና፣ ለግብርናና ለኃይል አቅርቦት ዘርፎች መጠቀም እንደምትፈልግ ገለጸች

ሐምሌ 21/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለጤና፣ ለግብርና እንዲሁም ለኃይል አቅርቦት ዘርፎች መጠቀም እንደምትፈልግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከሩሲያው የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ አሌክሴይ ሌካቼቭ ጋር በኢትዮጵያ ለሚተገበረው የኒውክሌር ልማት ፍኖተ ካርታ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ጎን ለጎን የተፈረመው የአሁኑ የአፈጻጸም ሰነድ ከዚህ ቀደም የተፈረመውን ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባትና በዘርፉ ግልፅ አሰራርን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የሩሲያው የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ አሌክሴይ ሌካቼቭ በስምምነቱ ወቅት በአቶሚክ ሳይንስ ላይ የኢትዮያዊያን ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የስምምነቱ ቀዳሚ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።

ተቋሙ በ8 አገራት 33 የኒውክሌር ምርምር ማዕከላት ግንባታ ላይ እየሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ለስምምነት የበቃው የኒውክሌር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያ በዘርፉ የህክምና፣ የግብርና፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና በምርምር ላይ ያላትን አቅም ለማዘመን ያስችላታልም ነው የተባለው።