መስከረም 27/ 2013 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ በተጻረረ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት እስራኤል ድጋፍ እንድትሰጥ ጠየቁ፡፡
ሚኒስትሩ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ ልዑክ አምባሳደር ባርሊ ሻሮን ከተመራው የእስራኤል ከፍተኛ የመንግስት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያይተዋል፡
በውይይታቸው በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸው፣ በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ደመቀ ሁለቱ ሀገራት በመከባበርና እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በማውሳት፤ ይህንን ምቹ ሁኔታም በሀገራቱ መካከል በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀም አንደሚያስፈለግ ጠቁመዋል።
አክለውም በግብርና ምርታማነት፣ አቅም ግንባታ፣ በሰላም እና ደህንነት ዘርፎች የጋራ ትብብሮች እንዲጠናከሩ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ አዲስ መንግስት መመስረቱን አስመልክቶም ለልዑካን ቡድኑ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ባርሊ ሻሮን በበኩላቸው፣ መረጃውን ለእስራኤል መንግስት እንደሚያስተላልፉ በመግለጽ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አጠናክራ እንደምታስቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡