‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) ‘ኤችአር 6600’ እና ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ለማድረግ መንግሥት ከዳያስፖራ አባላት ጋር በመሆን የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደገለጹት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ ከጅምሩ አንስቶ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን ሠላምና ልማት ጭምር አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት ገለጻ መደረጉን ጠቁመዋል።

በተለይም በችግር ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ጥረት በማስተጓጎል ሰብዓዊ ቀውሱን እንደሚያጎላው ጭምር ለማስረዳት መሞከሩን ገልጸዋል።

ረቀቅ ሕጎቹ ለበርካታ ዓመታት በወዳጅነት የዘለቀውን የኢትዮጵያና የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያበላሸውም የማስገንዘብ ሥራ በመንግሥትና በዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኩል መሠራቱን ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው የሚያደርገውን ጥረት አሁንም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብና ለጋሽ ሀገራት ወደ ትግራይም ይሁን ወደ ሌሎቹ ክልሎች የሚያቀርቧቸው የሰብዓዊ ድጋፎች ተጠናረክው መቀጠላቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ከችግሩ ጋር የሚመጣጠን ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን አንስተው የሚደረገው ድጋፍ መጠን ከፍ እንዲልም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በተለይም የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗንም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጋር በመሆን የቀጣናውን ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋገግጡ በርካታ ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!