ኤጀንሲው በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ተቋም ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው የተቋሙን ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የ2013 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እና መላው አባላት በተሳተፉበት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ኢመደኤ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት የሚያስችለውን ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ስኬት ለሰው ኃይል ልማት፣ ለቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እና ለአሠራር ሥርዓት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ስትራቴጂክ መሠረቶችን በተመለከተም ቴክኖሎጂና የዕውቀት ባለቤትነት፣ መሠረተ ልማት፣ ተቋማዊ ልህቀት፣ ትብብርና ቅንጅት እንዲሁም ፖሊሲ፣ ህግና ስታንዳርድ ማዕቀፎች የትኩረት መስኮች እንደሆኑ መግለጻቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡