ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት የ285 ብሔራዊ ደረጃዎችን አፀደቀ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት የ285 ብሔራዊ ደረጃዎችን አፀደቀ።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ምክር ቤቱ ደረጃዎቹን ያጸደቀው በ6 ዘርፎች ተዘጋጅተው ከቀረቡለት 289 ረቂቅ ደረጃዎች መካከል መሆኑን አስታውቋል።

በግብርና ምግብ ዘርፍ 18፣ በመሰረታዊና አጠቃላይ ዘርፍ 28፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች 72፣ በኮንስትራክሽን ሲቪል ኢንጅነሪንግ 79፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል 79 እንዲሁም በአካባቢና ጤና ደህንነት 19 ደረጃዎችን ምክር ቤቱ አጽድቋል።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን ከኮቪድ-19፣ ከዲጂታል የፋይናንስ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል እና ከአካባቢ ጥበቃና ቆሻሻ አወጋገድ ጋር ግንኙነት ያላቸው ደረጃዎች በተለየ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል።

ደረጃዎቹ 148ቱ በአዲስ፣ 44ቱ እንደገና በመከለስ እና 93ቱ ደግሞ በፊት በነበሩት እንዲቀጥሉ ውሳኔ በማስተላለፍ እንዲጸድቁ መደረጉን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ ናቸው።

ደረጃዎቹ የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ሚናቸው ጉልህ  መሆኑንም ተናግረዋል።

አምራቾችና አገልግሎት ሰጭዎች የወጡትን ብሔራዊ ደረጃዎች ከግምት በማስገባት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደረጃዎችን በማዘጋጀት አምራቾችና አገልግሎት ሰጭዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መረጃዎችን ያቀርባል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት 11 ሺህ 409 ብሔራዊ የምርት ደረጃዎች እንዳሏት ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።