ኤጀንሲው በ60 ተቋማት ላይ የተከሰቱ የሳይበር ደህንነት ክፍተቶች እንዲታረሙ አደረገ

ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) –የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በ2013 ዓ.ም ባደረገዉ የሳይበር ደህንነት ፍተሻ 60 በሚሆኑ ተቋማት ላይ የተፈጠሩ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን መለየት መቻሉንና ክፍተቶቹም እንዲታረሙ ማድረጉን ገለጸ፡፡

በኤጀንሲዉ የሳይበር ደህንነት ፍተሻ እና ግምገማ ዲቪዥን ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ወ/ጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀዉ በጀት አመት በ60 የመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ ጥልቅ የደህንነት ፍተሻዎች ተደርጓል።

ተቋማቱ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ፍተሻ የተደረገላቸው ሁሉም ተቋማት ክፍተት እንደተገኘባቸዉ የተናገሩት ሀላፊው፤ ይህ ማለት ክፍተት ያለበት ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት፣ የሰው ሃይል እና የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከተለዩት የሳይበር የደህንነት ክፍተቶች መካከል 84 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን 8 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ እንዲሁም 6 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳታቸው ዝቅተኛ የሚባሉ ክፍተቶች እንደነበሩ ሃላፊዉ መናገራቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እነዚህን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን ለመቅረፍ ተቋማቱ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባቸዉ አሳስበው፤ ተቋማቱ በኤጀንሲዉ የተሰጣቸዉን ምክረ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ክፍተቶቹን ማስተካከል፣ ማንኛውም ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት ከመተግበሩ በፊት የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግለት ማድረግ፣ ተቋማቱ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሰራተኞቻቸውን ንቃተ ህሊና ማሳደግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

“ተቋማቱ ከኤጀንሲው ጋር ተቀራርቦ መስራት እና አስፈላጊውን እገዛ መጠየቅ ይገባቸዋል” ያሉት ሃላፊው፤ “ተቋማቱ አገልግሎት እየሰጡበት የሚገኙትን የሳይበር ደህንነት ስርዓቶች ቢያንስ በዓመት አንዴ የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግላቸው ማመቻት ይገባቸዋል” ብለዋል።