ኤጀንሲው የመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበት 20.6 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን አስታወቀ

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – የመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20 ነጥብ 6 ከመቶ ከፍ ብሎ መታየቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በየወሩ የሚያወጣውን የዋጋ ግሽበት መረጃ ሁኔታ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በእህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም የቀጠለ ሲሆን፣ ለምግብ ዋጋ ግሽበት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
የመጋቢት ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ22 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጿል።
“በተጨማሪም አትክልትና ጥራጥሬ ዓይነቶች የዋጋ ጭማሪ አስመዝግበዋል” ብሏል።
በሌላ በኩል የምግብ ዘይት፣ ቅመማ ቅመም በርበሬ፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ድንችና ቡና የዋጋ ጭማሪ በዚህም ወር በመቀጠላቸው ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ በያዝነው ወርም ከፍ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ18 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ፈጣን ዕድገት አሳይቷል፡፡
ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (ሲሚንቶና የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ ህክምና፣ ትራንስፖርት (ነዳጅ) እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው መሆኑ ተገልጿል፡፡
አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በ2 ነጥብ 9 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በማነፃፀር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን የሚያሳይ መሆኑም ተጠቁሟል።