እነዚህ እግሮች…….

እነዚህ እግሮች ላለፉት 22 አመታት በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ናቸው፡፡ ከፖርቹጋል እስከ እንግሊዝ፣ ከስፔን እስከ ጣሊያን ብሎም እስከ ሳውዲ እየተመላለሱ የበረኞች ራስ ምታት፣ የተከላካዮች ቅዠት ሆነዋል፡፡

እነዚህ እግሮች በሮኬት ፍጥነት ልክ ተተኩሰው የሄዱ ኳሶችን ያስወነጨፉ እግሮች ናቸው። እ.ኤ.አ በ2009 ማንችስተር ዩናይትድ እና ፖርቶ በነበራቸው ጨዋታ ያስቆጠሩት ፈጣን ግብ ይታወሳል፡፡ እንደ ስፖርት ሲቲ መረጃ መሰረት ደግሞ እነዚህ እግሮች በሰዓት እስከ 104.6 ኪ.ሜ ርቀት መጓዝ የሚችሉ ጠንካራ ምቶችን መምታት ይችላሉም ብሏል፡፡

እነዚህ እግሮች እንደ ሮኬት ኳስ ማስወንጨፍ ብቻም አይደለም የሚችሉት፡፡ እንደ ሮኬት ወደ ላይ መተኮስም ጭምር እንጂ፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ሪያል ማድሪድ ከማንችስተር የናይትድ ጋር በነበረው ጨዋታ 2.93 ሜትር ከፍታ በመዝለል አለምን ያስደነቁ ናቸው፡፡

እነዚህ እግሮች ፈጣንም ናቸው፡፡ በሩሲያው የአለም ዋንጫ ከስፔን ጋር በነበራቸው ጨዋታ በሰዓት 40 ኪ.ሜ በሚደርስ ፍጥነት ተፈትልከዋል፡፡

እነዚህ እግሮች ከ800 በላይ ግቦችን ያስቆጠሩ ከ5 በላይ ባላንዶሮችን ያስገኙ የታሪክ ተመስጋኝ እግሮች ናቸው፡፡

ትጋትን ከፅናት ጋር፣ ጥንካሬን ከልምምድ ጋር የያዙና የትውልዱን የእግር ኳስ ዘመን ያሳመሩ እግሮች ናቸው፡፡ የክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶስ ሳንቶስ አቪየሮ እግሮች!

ተጫዋቹ ከሳምንት በፊት በኢንስታግራም ገጹ ያጋራው ይህ ምስል ደጋፊዎቹንም ሆነ የእግር ኳስ ተመልካቹን ያነጋገረና ያስደነገጠ ነበር፡፡ ለሰራቸው ገድሎችና ላሳያቸው ክህሎቶች ምስጋና ያቀረቡ እንዳሉ ሆነው፤ አሁን እንደዚህ አብጠውና የተጎዱ መስለው መታየታቸው ስጋት ውስጥ የከተታቸውም አሉ፡፡

የሆነው ሆኖ እነዚህ እግሮች ደጋፊዎች ጮኸው የዘምሩላቸው፣ የተቃራኒ ቡድን በረኞች የማይረሷቸው፣ ከ20 አመታት በላይ በእግር ኳስ ላይ የነገሱ፣ የዘመኑ እግር ኳስ ተመልካቾች የሚያመሰግኗቸው የ39 አመቱ የCr7 እግሮች ናቸው፡፡