አፍሪካን ለማስተሳሰር ትልቅ አቅም ያለው ቡና

በአፍሪካ 25 ሀገራት በቡና አምራችነታቸው ይታወቃሉ። በሀገራቱ በገጠር ከሚኖረው ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ 56 በመቶ የሚሆነው ኑሮውን ከቡና ጋር ያደረገ ነው።

በአህጉሩ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ምርት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘውን ድፍድፍ ነዳጅ ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ የቡና ምርት ይጠቀሳል።

የቡና ምርት የአፍሪካ የነፃ ንግድ ትስስር አንዱ የስትራቴጂ ሸቀጥ እንዲሆን በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተወስኗል።

በሁለተኛው የአስር ዓመት እቅድ ትግበራ የአፍሪካን የ2063 አጀንዳ እንዲያሳካ ግብ ተጥሎበታል። በፀደቀው የአፍሪካ ንግድ ትስስር ውሳኔ መሰረት ቡናን ወደ ጎረቤት አፍሪካ ሀገራት ለመላክ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ተብሏል። በአፍሪካ ቀዳሚ የቡና አምራችና ላኪ የሆነችው ኢትዮጵያም ተጠቃሚ ለመሆን ምን እየሰራች ነው ሲል አዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን ከቡና ላኪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

                      የቀርጫንሼ ትሬዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ እስራኤል ደገፍ

የቀርጫንሼ ትሬዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ እስራኤል ደገፍ የአፍሪካ የነፃ ንግድ ትስስር  ጠቀሜታው አብዛኛውን የአፍሪካ ሀገራት የአንደኛው ምርት አንደኛው ጋር የመሸጥ እድላቸው በጣም ዝቅተኛና እርስ በርስ የምናደርጋቸው የንግድ ዝውውሮች በጣም የወረዱ ከመሆናቸው አንፃር ያንን ለማሳደግ እንደ አፍሪካ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።

                                                የሞየ ቡና እና ተጋና ቶላ እርሻ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ውብሸት አሃዱ

የሞየ ቡና እና ተጋና ቶላ እርሻ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ውብሸት አሃዱ አብዛኛውን ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ የምንነግድበት ቦታ አፍሪካ ውስጥ አልነበረም፤ በተለይ ቡናችንን ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አሜሪካ ነበር የምንልከው ብለዋል። አፍሪካዊያን እርስ በራሳችን እዚሁ መነገድ ከቻልን አንድ ትልቅ የገበያ እድል ይኖረናል ነው ያሉት።

“ቡና ብቻም ሳይሆን በጠቅላላው ሸቀጥ በምንላቸው ነገሮች ውስጥ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ልምድ የለም። ጎረቤት ያሉትን ሀገራት ራሱ እያዳረስን አይደለም። እሱን ስንመለከት ትልቅ የገበያ እድል ነው። በቡናም ከጀመርነው በሌላ ገቢዎቻችንም ላይ እንጠናከራለን ብዬ አምናለሁ” በማለት አሀዱ ውብሸት ተናግረዋል።

                               የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ግዛት ወርቁ

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ግዛት ወርቁ በበኩላቸው የተቆላ፣ የተፈጨ እና ያለቀለት ቡና አብዛኛዎቹ የማግረቭ ሀገራት እነ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ ከአውሮፓ ነበር የሚገዙት ሲሉ ገልጸውልናል። ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት የተቆላ ቡና የሚገዙ አሉ ያሉት ግዛት ወርቁ የቡና ገበያ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ነው የሚባል ባይሆንም ግን ያለውን ገበያ በመጠቀም መስራት ከቻልን ለኢትዮጵያ ጥቅም ያመጣል ብለዋል።

ከአፍሪካ ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና ምርት ውስጥ 39 በመቶውን የምትሸፍነው ኢትዮጵያ ናት። የቡና ምርት ከአህጉር ውጭ በስፋት ይሸጣል እንጂ በአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ ግብይት አነስተኛ የሚባል ነው። ነገር ግን አሁን ላይ የቡና ምርት የአህጉሩ አንዱ ስትራቴጂክ ሸቀጥ በመሆኑ ትልቅ የገበያ እይታን የሚፈጥር ነው ይላሉ የቡና ላኪዎቹ።

ከቱኒዝያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በቡና ንግድና ሌሎች ሸቀጦችን አብረን መስራት ከጀመርን ቆይተናል የሚሉት ላኪዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ የንግድ ግንኙነቱና ተሳታፊነቱ በሌሎች ግብዓቶች እያደገና እየጨመረ የመጣ መሆኑን ያነሳሉ። በአዲሱ ስትራቴጂክ መንገድም ከዚህ የበለጠ የሚጠናከር ይሆናል ብለዋል።

እንደ ደቡብ አፍሪካና ቱኒዝያ ያሉ የቡና ገዢ ሀገራት በቀጥታ ከኛ ጋር መስራት ጀምረው ትልቅ ለውጥ እያደረግን ነው፤ በየዓመቱ እያደገና እየጨመረ የሚገኝ ሂደት እውን እያደረግን ነው ሲሉም ይናገራሉ።

የንግድ ትስስሩ ከቡና ንግድ ባለፈ ይዞት የሚመጣው ጥቅም ሰፊ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን የሚያነሱት የዘርፉ ተዋንያን በአህጉሪቱ የሚስተዋለው የመሰረተ ልማት ችግር፣ የፖለቲካ ቀውስ፣ የመርከብ ትራንዚትና ሌሎችም ችግሮች ተዳምረው መሰናክል እንዳይሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ።

በሰማኸኝ ንጋቱ