እንግሊዝ በ5 የሩሲያ ባንኮች ላይ ማዕቀብ ጣለች

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) ሩሲያ የዩክሬንን ሉኣላዊ ግዛት ጥሳለች በሚል እንግሊዝ በሩሲያ 5 ባንኮች ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች፡፡

አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይና ሌሎችም ማዕቀብ እንደሚጥሉ እየዛቱ ነው።

እንግሊዝ ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ሀብት ባላቸው ሩሲያዊያን ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል የገለጸች ሲሆን ማዕቀቡ በእንግሊዝ ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስ እንደምታግድ የአንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ውስጥ ላሉ ተገጣይ ግዛቶች እውቅና መስጠቷን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊያን ማዕቀብ እንደሚጥሉ እየገለጹ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ፑቲን በምስራቅ ዩክሬን ለሚገኙ ተገንጣዮች እውቅና መስጠታቸው ዓለም ዐቀፍ ውግዘት ያስከተለባቸው ሲሆን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተገንጣዮቹ ግዛቶች ውስጥ የሚከናወኑ የአሜሪካ የቢዝነስ (ንግድ ሥራ) እንቅስቃሴ እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

ፈረንሳይ እና ጀርመንም በሩሲያ ላይ ማእቀብ ለመጣል የተስማሙ ሲሆን እንግሊዝ እና አሜሪካም ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ሶሪያ በአንፃሩ የሩሲያን ውሳኔ እንደምትደግፍ በፕሬዝዳንት በሽር አልአሳድ በኩል አሳውቃለች።

ከዩክሬን የኔቶ አባልነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሩሲያና ዩክሬን የገቡበት እሰጥአገባ በርካቶችን ለሁለት የከፈለ ውጥረት ውስጥ አስገብቷል።