ከመጠን በላይ ጨው በመመገብ በዓመት የበርካታ ሰዎች ህይወት ይቀጠፋል- የዓለም ጤና ድርጅት

መጋቢት 1/2015 (ዋልታ) ከመጠን በላይ ጨው በመመገብ በዓመት የበርካታ ሰዎች ህይወት እንደሚቀጠፍ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት አንድ ሰው በአማካይ በቀን መመገብ ያለበት የጨው መጠን 5 ግራም ቢሆንም አንድ ሰው በቀን በአማካይ እየተመገበ ያለው የጨው መጠን 10.8 ግራም እንደሆነ መረጃው አመላክቷል፡፡

በዚህም አንድ ሰው በቀን መመገብ አለበት በሚል የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው መስፈርት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን በርካታ ሰዎች ለልብ፣ ስትሮክ እና ሌሎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየተዳረጉ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ይህንን ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ ሀገራት አጠቃላይ የጨው አጠቃቀም ቅነሳ አስገዳጅ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የዓለም የጤና ድርጅት እየወተወተ ይገኛል፡፡

የጨው አጠቃቀም ቅነሳ አስገዳጅ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት ዘጠኝ ሀገራት ብቻ ናቸው ያለው ድርጅቱ ሀገራት የጉዳዩን አሳሳቢነትን በመረዳት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጡ ይገባል ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2025 ሰዎች የሚጠቀሙትን የጨው መጠን 30 በመቶ ለመቀነስ የታቀደ ሲሆን ከፍተኛ ወጪ ቆጣቢ የጨው ፍጆታ ቅነሳ ፖሊሲዎችን በመተግበር በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 7 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ህይወት መታደግ እንደሚቻል መረጃው አመላክቷል፡፡