ከሱዳን በአልምሃል ሰርጎ ገቡ የሕወሓት ቅጥረኛ መደምሰስ

ኮ/ል ሰይፈ ኢንጊ

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) ከሱዳን በአልምሃል ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የጁንታው ቅጥረኛ ኃይል በጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ተደመስሷል፡፡

በዚህ ተልዕኮ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ በሱዳን ሰርጎ ለመግባት የሞከሩ ሀምሳ የሽብር መልዕክተኞችና የጁንታው ቅጥረኞች ሲደመሰሱ ከ70 በላይ ቆስለዋል፡፡

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረኃይል ኮማንድ ፖስት የኦፕሬሽን ዘርፍ አሰተባባሪ ኮ/ል ሰይፈ ኢንጊ ቅጥረኛው የተለያዩ ፀረ ሰው እና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ የሞከረ ቢሆንም፤ መቋቋም ተስኖት ተበታትኗል ብለዋል፡፡

ጠላት አሳቻ ሰዓት ጠብቆ አካባቢውን ለማተራመስ ቢንቀሳቀስም የጠላትን እንቅስቃሴ ከመነሻው በንቃት ሲከታተሉ የነበሩት የመከላከያ ሰራዊቱ ክፍሎች ተቀናጅተው እርምጃ እንደወሰዱበት ነው የገለጹት፡፡

የጠላት ሃይል የቻለውን ያህል ለመከላከል ቢሞክርም በጀግናው ሰራዊት የበላይነት ተወስዶበት የተረፈው ሃይል አግሬ አውጪኝ በማለት መፈርጠጡን ኮ/ል ሰይፈ ተናግረዋል፡፡

የጥፋት ሃይሉ ሲጠቀምባቸው እና ለእኩይ ስራው ሲያዘጋጃቸው የነበሩ ቀላል እና ከባድ የቡድን መሳሪያዎች ፣ ፈንጂዎች የወደሙ ሲሆን÷ የተቀሩት በጀግናው ሰራዊት ቁጥጥር ስር ገብተዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በግንባር ድል አልቀና ሲለው አብዛኝው ጦር ወደ ሰሜኑ ክፍል አቅንቷል በሚል ከታሪካዊ ጠላቶች ተቀናጅቶ የህዳሴ ግድቡን ስራ ለማስተጓጎልና ለማጥቃት ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ስዓት በአካባቢው ጀግናው የመከላከያ ሃይል፣ እግረኛና ሜካናይዝድ ክፍለጦሮች እንዲሁም የክልል ልዩ ሐይሎች አስፈላጊውን ዝግጁነት በማረጋገጥ ግዳጃቸውን እየፈፀሙ እንደሚገኙ ኮ/ል ሰይፈ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡