ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ


ሀገር በሰላምና በህዝቦች አንድነትና ኢትዮጵያዊ ወንድማዊነት ካስማ የተመሰረተች እንጂ ማንም ፅንፈኛ ተነስቶ በአንድ ቀን ጀምበር የሚያፈርሳት አይደለችም!!

ህገ-መንግስቱን ለመናድና ሀገሪቱን ወደ ቀውስና ትርምስ ለመንዳት የሚደረገውን ማንኛውንም የፅንፈኛ ቡድኖችን ጭፍን ጥላቻና አሸባሪነት የክልላችን መንግስት በፅኑ ያወግዛል።

ሀገራችን ከለወጡ መንግስት ወዲህ ወደ ተሻለ ልማትና ሁለንተናዊ ዕድገት የምታደርገውን ጉዞ ለማደናቀፍ ፅንፈኛ ቡድኖች በጭፍን ጥላቻ ተነሳስተው ሀገራችንን ወደ ቀውስና አዘቅት ለመክተት ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ነፍጥ አንግበው ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

ለዚህም ማሳያ እነዚህ ፅንፈኛ ቡድኖች በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ማለትም በአማራ ክልል ህብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመናድና ድብቅ የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት እንዲሁም የአማራን ህዝብ በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዳት፣ በማወናበድና በህዝቡና በመንግስት መካከል መቃቃርን በመፍጠር የሽብር ጦርነት በይፋ ከፍተዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተጠነሰሰውን ሴራ ለማብረድና ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት የተሳካ እንዳይሆን ፅንፈኛ ቡድኖቹ ጠብመንጃ አንግበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ሰራዊቱ ከዚህ ቀደም በሀገራችን ላይ በውጪ ሀይሎችና በሀገር ውስጥ ባንዳዎች በሉዓላዊነታችን ላይ የተቃጡ ሴራዎችን በፅናት በመታገል ያከሸፈና የሀገራችንን ዳር ድምበር ያስከበረ እና እያስከበረም ያለ የሀገር ምሰሶ መሆኑን እንኳን ወዳጅ ጠላትም ያውቀዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ፅንፈኛ ቡድኑ የሰራዊቱን ስም ለማጠልሸትና የሀገሪቱን አንድነት ለመናድ ከሀገራችን ጠላቶች ጋር በማበር ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የአማራ ክልል ህዝብ መብቶችና ጥቅሞች ከሌላ ኢትዮጵያውያን ጋር የተሳሰሩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ፅንፈኛ ቡድኑ ለፕሮፓጋንዳው እንዲመቸው የአማራ ህዝብ ተነጥሎ የተጨቆነ ለማስመሰል የሚያደርገውን ሀሰተኛ አሉባልታ የክልላችን መንግስት በፅኑ ያወግዛል።

ይህ ግጭት በጦርነት ውስጥ የቆየውን የአማራን ህዝብ ለማሰቃየትና ወደ ባሰ እልቂትና እንግልት ለመዳረግ የታለመ መሆኑ እሙን ነው። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው ዴሞክራሲያዊ መንገድ በተከተለ አካሄድና ሚዛን ሊደፋ በሚችል በሳል ሀሳብና በጠረጴዛ ውይይት እንጂ በትጥቅ ትግልና በሽብር የሚመለስ ጥያቄ አይኖርም።

እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች ከድርጊታቸው ታቅበው ወደ ሰላም የማይመለሱ ከሆነ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ህግን ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃ የክልሉ መንግስት ይደግፋል።

በተጨማሪም የሀገራችን መንግስት የህዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዲከበርና ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና አንድነት እንዲሰፍን የሚያደርገውን ማንኛውንም ተግባር የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚደግፍና ከሀገራችን መንግስት ጎን የሚቆም መሆኑን እንገልጻለን።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም
ሀዋሳ