መዲናዋ የስነምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እንደሌላት ተገለጸ የስነምግባር እና ጸረ-ሙሽና ኮሚሽን እንደሌላት ተገለጸ

የአዲስ አበባ ከተማ የማቋቋሚያ ቻርተር  የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በከተማዋ ተቋቁሞ እንዲያስተዳድር በህግ ቢደነገግም ከተማዋ ግን እስካሁን የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እንደሌላት ተገለጸ፡፡

የፌዴራል ስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከከተማና ከክፍለ ከተማ ከተውጣጡ አመራሮች ጋር አዲስ በተዋቀረው የስነ ምግባር  መከታተያ አደረጃጀት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

የፌዴራል ስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጸጋ አረጋ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሶስት አመታት ምከንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በከተማ፣ በክፍለ ከተማና ወረዳ አደረጃጀት የነበሩ የስነምግባር መከታተያ መዋቅሮች ፈራርሰው ቆይተዋል ብለዋል፡፡

የፌደራል ስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከተሞች በራሳቸው ህግ ማእቀፍ አቋቁመው የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ጉዳዮችን እንዲከታተሉ መወሰኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጸጋ፣ ለጊዜው በየአደረጃጀቱ የተቋቋመው የስነምግባር መከታተያ ስርዓት በርካታ ስራዎችን እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ የተደራጀ የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን መከታተያ አደረጃጀት ባለመኖሩም በከተማዋ የህዝብ ሀብት ያለአግባብ እንዲመዘበር እና ብልሹ አሰራር እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት  ሰጪ  ተቋማት አስተባባሪ ዣንጥራር አባይ ሙስና ከጊዜያዊ ጥቅም ሊያልፍ እንደማይችል ገልጸው፣ በከተማዋ የተዋቀረው የስነምግባር መከታተያ አደረጃጀት ስራውን በተገቢው መልኩ እንዲያከናውን የሁሉም የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ሚና ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን መዋቅር በድጋሚ ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑም በአዲስ መልክ የስነምግባር መከታተያ አደረጃጀት መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ ከፍተኛ ሀብት በሚንቀሳቀስባት አዲስ አበባ ከተማ እስካሁን የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አለመኖሩን ተከትሎ ሙስና እንዲንሰራፋ እድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ከከተማና ክፍለ ከተማ የተውጣጡ አመራሮች በውይይት መድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡

እስከ ታህሳስ 30 ሁሉም የመንግስት ሰራተኞችና የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡም መመርያ ወጥቷል፡፡

 

(በመስከረም ቸርነት)