መጋቢት 25/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ቢሮ በማህበር ተደራጅተው ቤት ለመገንባት በመመዝገብ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በአምስት ክፍለ ከተሞች መሬት ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር አማራጭ የቤት ልማት አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ታምራት ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ቢሮው በከተማዋ የሚታየውን ሰፊ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮችን ይዞ እየተንቀሳሰ ነው።
በቅርቡ በ20/80 እና በ40/60 ፕሮግራም ሙሉ ክፍያ ከፍለው ቤት ለማግኘት እየተጠባበቁ ላሉና 70 በመቶ መክፈል የሚችሉ ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው መኖሪያ ቤት መገንባት የሚችሉበትን አማራጭ ይዞ ቀርቧል። ለግንባታው የሚሆን መሬት በአዲስ ከተማ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በኮልፌ ቀራንዮና በቦሌ ክፍለ ከተሞች ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የመጀመሪያ ዙር ከ100 እስከ 130 ማህበራት ለማደራጀትና 10 ሺህ የሚደርሱ ቤት ፈላጊ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምዝገባው በተጀመረ አራት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ 3000 በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።
ይህም ሰዎች በራሳቸው አቅም ለመገንባት ያላቸውን አቅምና ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።