በአንድ ሳምንት ከ53.7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸው ተገለጸ

መጋቢት 25/2013 (ዋልታ) – ከመጋቢት 16 እስከ መጋቢት 23/2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት በ53 ሚሊየን 795 ሺህ 644 ብር የሚገመቱ ዕቃዎች በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ እና ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች 40 ሚሊየን 300 ሺህ 334 ብር የሚገመቱ ዕቃዎች ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 13 ሚሊየን 495 ሺህ 310 ብር የሚገመቱ ዕቃዎች ደግሞ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ በተለያዩ የጉምሩክ ኬላዎች የተያዙ መሆናቸው ተገልጿል።
ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ የጦር መሣሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ አደንዛዥ እፆች፣ የግብርና ምርቶች፣ ምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች፣ አልባሳት እና ጫማዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ኮስሞቲክስ፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች ይገኙበታል፡፡
ዕቃዎቹ የተያዙት በጉምሩክ ሠራተኞች እና በፀጥታ አካላት ርብርብ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያጓጉዙ የነበሩ 35 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡