ከተማ አስተዳደሩ ”የአንድ ቤተሰብ ለአንድ ህጻን ፕሮግራም” መርኃ ግብርን አስጀመረ


መስከረም 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ”የአንድ ቤተሰብ ለአንድ ህጻን ፕሮግራም” መርኃ ግብርን ለ100 ህጻናት ዘላቂ ድጋፍ በመስጠት አስጀመረ።

ፕሮግራሙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የMWS ትሬዲንግ ባለቤት ማናዬ ሰንደቁ ተፈራርመዋል።

መርኃ ግብሩ ህጻናት አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘት እንዲችሉ ከማደረግ በሻገር ዘላቂ ድጋፍ እንዲያገኙ ያስችላል ነው የተባለው፡፡

”የአንድ ቤተሰብ ለአንድ ህጻን ፕሮግራም” ተጠቃሚ ከሆኑት በተጨማሪ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በክረምቱ ወራት ለ330 ህፃናት ከ3 ወር እስከ 3 ዓመት ድጋፍና ትስስር የተፈጠላቸው ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ 430 ህፃናት የዚህ በጎ መርኃ ግብር ተጠቃሚ እንደሆኑ ተገልጿል።

ከተማ አስተዳደሩ በሰው ተኮር ስራዎች 750 ህፃናትን በጉዲ ፈቻና ባሉበት ሆነው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት ሁሉ ምን ያህል ሰው ተኮር ናቸው የሚለው በትኩረት ይታያል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዛሬው ድጋፍ በአንድ ባላሀብት የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከንቲባዋ አክለውም በመንግስት የተያዘው ትውልድን መገንባት በመዲናዋ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ትውልድ ላይ በትኩረት መስራት የነገ አገርን ተስፋ ዛሬ መስራት በመሆኑ አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል ብለዋል።

ይህን ድጋፍ ያደረጉት የኤም ደብሊው ኤስ ትሬዲንግ ባለቤት ማናዬ ሰንደቁ አማካይነት 100 ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ እንዲማሩ እና ድርጅቱ በዘላቂነት ድጋፉን እንደሚቀጥል ባለሀብቱ ተናግረዋል።

በግዛቸው ግርማዬ