ከተማ አስተዳደሩ የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምና የ2014 መሪ እቅድ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው

ሐምሌ 28/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እና የ2014 መሪ እቅድ  ላይ ውይይት እያካሄዱ ይገኛል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተደደሩ ከፍተኛ አመራሮች በ2013 በጀት ዓመት የተገኙ ውጤቶችን እና የታዩ ጉድለቶች እንደሚገመግሙ ገልጸው ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ አመራሩ ግንዛቤ መያዝና ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በምርጫው የሰጠን ድምፅ  በተሻለ ብቃትና በታማኝነት እንድንፈጽም  አመራሩ አቅሙ ተገንብቶ፣ ጉድለቶቹን አርሞ የተሰጠውን ሥራ በብቃት መፈጸም አለበት ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በ2014 በጀት ዓመትም በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን ተቋማዊ አሰራርን መሠረት ባደረገ መልኩ በማጠናከር እና በህብረተሰቡ በኩል የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል።

በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ባለው ውይይት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣  በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ አለሙ፣ የሴክተር ተቋማት፣ የሁሉም ክፍለ ከተሞች እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡