ከተማ አስተዳደሩ 6ቱ የጳጉሜን ቀናት በተሰጣቸው ስያሜና ተግባር ለማክበር መዘጋጀቱን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትዓለም መለስ

ነሐሴ 27/2015 (አዲስ ዋልታ) ስድስቱ የጳጉሜን ቀናት በተሰጣቸው ስያሜና ተግባር መሰረት በከተማ ደረጃ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትዓለም መለስ በሰጡት መግለጫ የአገልጋይነት ቀን በሆነው ጳጉሜን 1 ለአንጋፋ መምህራንና ለጤና ባለሙያዎች ምስጋናና እውቅና የመስጠት ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን እንዲሁም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የመስዋዕትነት ቀን በሆነው ጳጉሜን 2 በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ተቋማት ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት በማከናወን ለመከላከያ ሰራዊት እና ፀጥታ አካላት የማክበር ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድና የደም ልገሳ መርኃ ግብር እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች የተገነቡ 860 ቤቶች ለአቅመ ደካሞች እንደሚተላለፉ፣ ለ3 ሺሕ ሰዎች ማዕድ የማጋራት መርኃ ግብር እንደሚከናወንና በከተማ አስተዳደሩ የተገነባና 20ኛው የምግብ ማዕከል የሆነው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል እንደሚመረቅ ገልጸዋል።

አምራችነት ቀን በሚል በተሰየመው ጳጉሜን 4 የሀገር ውስጥ ምርቶች በተለያዩ የገበያ ባዛርና ኤግዚቢሽን ማዕከላት የሚከፈቱ ሲሆን የትውልድ ቀን ተብሎ በተሰየመው ጳጉሜን 5 ደግሞ የመምህራንና እና የወላጆች የውይይት መድረኮች እንደሚከናወን ኃላፊዋ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

አብሮነት ቀን በሆነው ጳጉሜን 6 ስለ አብሮነት የውይይት መድረኮች ይከናወኑበታልም ነው የተባለው።

በትዕግስት ዘላለም