ከተሞቻችን – ሚዛን አማን

የሚዛን አማን ከተማ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንዷ መቀመጫና የቤንች ሸኮ ዞን ዋና መቀመጫ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ከርዕሠ መድናችን አዲስ አበባ በ568 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ስተሆን በ1930 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገራል።

ሚዛን አማን ከተማ የቀድሞ ሚዛን ተፈሪ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በንጉሱ አፄ ኃይሌ ስላሴ ዘመነ መንግሥት አከባቢውን እንዲያስተዳድሩ ተሹመው በተላኩት በእንደራሴው ፊታውራሪ አለማየሁ ፍላቴ መሆኑ ይነገራል፡፡

የንጉስ አፄ ኃይሌ ስላሴ ልደት እየተከበረ በነበረበት ወቅት ከተማዋ በመመስረቷ የልደት መታሰቢያ ለማድረግ እንደሆነም ታሪክ ይጠቅሳል።

በ1ሺሕ 451 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ላይ የምትገኘው ሚዛን አማን በአረንጓዴ መልክዓ ምድር የተሸፈነች እና ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት ከተማ ነች።

እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሚዛን አማን በዙሪያዋ ከፍተኛ የደን ክምችት ያላት ሲሆን ቡናን ጨምሮ፣ በፍራፍሬ እና በቅመማቅመም ምርቶች ትታወቃለች፡፡ የአረንጓዴ ልማት ፈርጥ ተብላም ትጠራለች።

የሚዛን አማን ከተማ በ2 ክፍለ ከተማ የተከፈለችና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማ ነች፡፡

በከተማዋ ከግል ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ከ5 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ፣3 ኮሌጆች እና የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ይገኛሉ።

ደረጃቸውን የጠበቁ ባለኮከብ እና ኢንተርናሽናል ሆቴሎችም በከተማዋ ይገኛሉ።

የ”ደንቢ” የሰው ሰራሽ ግድብ እንዲሁም 30 ሜትር ከፍታ ላይ እየተወረወረ የሚወርድ ውብና የተፈጥሮ ትዕይንት የሆነው የደንቢ ፏፏቴ ከሚዛን አማን ከተማ 8.5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የከተማዋ አንዱ የቱሪዝም መዳረሻዋ ነው።

በሀገሬው ቋንቋ “ሹንክተን” (የፍቅር ከተማ) በሚል የምትሞካሸው የሚዛን አማን ከተማ፣ ተቻችሎ በመኖር እና በእንግዳ አክባሪነቷ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ተብላም ትጠራለች።

በዚህች የፍቅር ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁና በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን። መልካም ሳምንት

በአዲሳለም ግደይ