ገንዘቡን ከወሰዱት ግለሰቦች መካከል 560 ሰዎች አልተገኙም

ከዛሬ ጀምሮም ማንነታቸው በባንኩ ማህበራዊ ትስስር ገፅ ይለቀቃል ተብሏል

ባንኩ ካጋጠመው ችግር ጋር ተያይዞ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘደንት አቤ ሳኖ በመግለጫቸው ባንኩ ባጋጠመው ችግር ምክንያት 801 ሚሊየን ብር ያለአግባብ ተወስዶ እንደነበር ገልፀዋል።

ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ከነበራቸው ውስጥ 9 ሺሕ 200 ያህሉ በፈቃደኝነት የወሰዱትን ገንዘብ መልሰዋል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም 223 ሚሊየን 475 ሺህ 369 ብር ተመላሽ መደረጉን አንስተዋል።

ከዚህ ባሻገር 5 ሺሕ 160 ያህል ግለሰቦች ደግሞ በፈቃደኝነት የወሰዱትን 148 ሚሊየን 21 ሺሕ 191 ብር በከፊል መመለሳቸውን አክለዋል፡፡

ወጪ ከተደረገው ገንዘብ በተወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ 44 ሚሊየን 668 ሺሕ 232 ያህል ገንዘብ ተመላሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

እንደ አጠቃላይ ባንኩ በአጠቃላይ ወጪ ከተደረገው ገንዘብ 78 በመቶ ያህሉን ገንዘብ ተመላሽ ማድረግ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡

ገንዘቡን ከወሰዱት ግለሰቦች መካከል 567 ሰዎች አልተገኙም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማህበራዊ ድረገፅ ማንነታቸው እንደሚለጠፍም ገልፀዋል።

በዙፋን አምባቸው