ከንቲባ አዳነች ሀገራዊ የለውጥ ጉዟችን እንዲቀጥል ስክነት ያስፈልገናል አሉ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) ሀገራዊ የለውጥ ጉዟችን እንዲቀጥል ስክነት ያስፈልገናል ሲሉ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ላለፉት ስድስት ቀናት “አዲስ ፖለቲካዊ እይታ – አዲስ ሀገራዊ እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል፡፡

በማጠቃለያው ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፈተናዎች ውስጥ ብናልፍም ምን ያህል በጥበብ እንደተመራንና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ተጉዘን ዛሬ ላይ መድረስ እንደቻልን ግንዛቤ የተወሰደበት እንደሆነ እናምናለን ብለዋል፡፡

በሀገራችን ባለፉት ዘመናት ለውጦች በሚገባ ባለመመራታቸው ምክንያት ተደናቅፏል ያሉት ከንቲባዋ ለዚህም ነው ስትራቴጂክ በሆነ አመራርና ፅናት ባይመራ ኖሮ ይህ ለውጥ እንደሌሎቹ  በመክሸፍ ራሱን ይደግም ነበር ብለዋል፡፡

በተለይ በዚህ ወቅት ሁሉም ፖለቲካ ተንታኝ ነኝ በሚልበትና ምክንያታዊ ያልሆነ የፖለቲካ ትንታኔና ድምዳሜ የሚሰጥበት በመሆኑ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ኑሮ ውድነትን በማቃለል በኩል ትኩረት በመስጠት የ90 ቀን እቅዶችን ለይተን አውርደናል ነው ያሉት፡፡

ይህንን ስናደርግ ተረጂነትን እያጎለበትን አይደለም ያሉት ከንቲባዋ ነገር ግን ሰው ተኮር በመሆናችን ሕዝባችን ዛሬን መኖርና ይህንን ወቅት መሻገር ስላለበት ነው ብለዋል፡፡

ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መስጠት እንዲሁም ለቱሪዝም መዳረሻነት አመራሩ በሚገባ  እንዲተጋ አሳስበው ከተማችን በምንም መልኩ መዳረሻ እንጂ መተላለፍያ አትሆንም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ አመራሮቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተከናወነ ያለውን የጓሮ አትክልት ልማት ተሞክሮ መጎብኘታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡