ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሀገር በቀል ምርቶች ዕውቅና ልንሰጥና አምራቾችን ልናበረታታ ይገባል አሉ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) በሀገራችን ምርት መኩራትን በመናገር ብቻ ሳይሆን ገዝተን በመጠቀም ለሀገር በቀል ምርቶች ዕውቅና ልንሰጥና አምራቾችን ልናበረታታ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

12ኛው የአዲስ አበባ የቴክኒክ፣ ሙያና ቴክኖለጂ ሳምንት አውደ ርዕይ ከንቲባዋ በተገኙበት በወዳጅነት ፓርክ ለጎብኝዎች እይታ ክፍት ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ልማት ቢሮ ‘’ሙያና ቴክኖሎጂ ለምርታማነት’’ በሚል መሪ ሃሳብ የከተማ ነዋሪዎችን የቴክኖሎጂ ፍላጎትና የልማት እንቅስቃሴ የሚደግፉ በቴክኒክ ሙያ ተቋም የተፈበረኩ ሀገር በቀል የፈጠራ ውጤቶች ዓውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ለተከታታይ ቀናት ለተጠቃሚዎች ክፍት አድርጓል፡፡

ከንቲባዋ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢንዱስትሪ፣ የፈጠራ ሥራና ቴክኖሎጂን የከተማ አስተዳደሩ ለሕዝብ የገባውን ቃል አንድ በአንድ ለመመለስ እንዲችልና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዓይነተኛ ቁልፍ መሣሪያዎች ናቸው ብለን አምነን ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በጋራ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በሀገራችን ምርት መኩራትን በመናገር ብቻ ሳይሆን ገዝተን በመጠቀም ለሀገር በቀል ምርቶች ዕውቅና ልንሰጥና አምራቾችን ልናበረታታ ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች የሀገርን ኢኮኖሚ ከቃላት ባለፈ በተግባር የምንደግፍበትም አይነተኛ መንገድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ክህሎት በራስ የመተማመን ምንጭ ነው፤ በራስ መተማመን ደግሞ ለፈጠራ ሥራዎች ሁሉ መክፈቻ ቁልፍ በመሆኑ ከችግሮቻችን ሁሉ በቶሎ ለመውጣት ሀገር በቀል የፈጠራ ሥራዎችን በሙሉ አቅማችን ልንደግፍ ይገባል ብለዋል።

ተጠቃሚዎች ለተከታታይ ቀናት ወዳጅነት ፓርክ እየመጡ ምርቶችን እንደየፍላጎቶቻቸው ገዝተው በመጠቀም አምራቾቸንና ሀገር በቀል ፈጠራን ማበረታታት እንዲችሉ ኤግዚቢሽንና አውደ ርዕዩ ክፍት መሆኑን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።