መጋቢት 1/2016 (አዲስ ዋልታ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የዐብይ ፆም ወራትን ከክፉ ኅሊና እና ተግባር የተለየን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጎ ነገርን ለመስራት በእጅጉ መበርታት ይጠበቅብናል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ የሚጀምረውን የአብይ ፆምን በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጾም እህልንና የእንስሳት ውጤቶችን ከመመገብ መከልከል ብቻ ሳይሆን ማናቸውን የሀጢያት ተግባር ላለማስተናገድ መራቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አክለውም “ስንጾም መገዳደልን፣ መጣላትን፣ መለያየትን፣ መገፋፋትን በሆነ ነገር መጐምጀትን እርም ብለን በመተው ዲያብሎስን የምናሸንፍበት የአሸናፊነት ኅሊና መላበስ አለብን” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ ታላቁን የዐብይ ፆም ሲፆም በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ እና ያለውን በማካፈል ሊሆን እንሚገባም አሳስበዋል።