ጀግና አስተዋሽ ፈረስኞች ማህበር…

#ሀገሬ

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቦች እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶች ባለቤት ነው። የዘንገና ጥርባ ሐይቆችን ጨምሮ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች፣ ቅርሶችና ሌሎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከነዚህም ውስጥ የትውልድ ጀግንነትን በመዘከር የሚታወቀው ታሪካዊው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ክብረ በዓል አንዱ ነው።

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በ1932 ዓ.ም በአምስት ዓመት የአርበኞች ተጋድሎ የጣሊያን ጦር ከተመታና ወረራው ከተቀለበሰበት የድል ማግሥት ጀምሮ እንደተመሠረተ ይነገራል፡፡

ከጦርነቱ መልስ በሰባት ሰዎች ተጠንስሶ በ33 አባላት እንደተመሠረተ የሚነገርለት የአገው ፈረሰኞች ማህበር አባላት ቁጥር አሁን ከ62 ሺሕ በላይ እንደደረሰ መረጃዎች ይጠቀማሉ።

ማህበሩ “የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማኅበር” የሚል ስም ያገኘው አንክሺ፣ ባንጂ፣ ዚጋሚ፣ አዚኒ፣ ኳኩሪ፣ ቻሪና ሚቲክሊ ከተባሉት ወንድማማቾች መሆኑም ይጠቀሳል፡፡

በየዓመቱ በጥር ወር በድምቀት የሚዘከረው ይህ በዓል በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ይከበራል፡፡ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥታዊ ሥርዓት ለውጦችን ተሻግሮ እስከአሁን የዘለቀው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ ክብረ በዓል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በየዓመቱ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ታጅቦ ይከበራል። በዓመታዊ ክብረበዓሉ ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ ባህላዊው የፈረስ ጉግስ ውድድር ነው።

የአገው ፈረሰኞች የፈረስ ጉግስ ውድድር ፆታ፣ ዕድሜና ሃይማኖት ሳይገድበው ሁሉም ፈረሱን ይዞ በዕለቱ በዓሉ ወደሚከበርበት ሥፍራ የምተምበት ሲሆን የተለያዩ ትርዒቶችን በማቅረብም የፈረሰኞችና የፈረሶች ድንቅ ብቃት ይታያል።

ይህ ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ውድድር ከአዊዎች ጋር ከፍተኛ ባህላዊ ቁርኝት ያለውም ነው። ለዓመታዊው የፈረስ ጉግስ ወድድር ተሳታፊዎች የተለያዩ ዝግጅቶችን ያደርጋሉ።

እንደብሔረሰቡ ባህል አንድ ሰው ፈረሰኛ ለመባል ፈረስ ሊኖረው እንደሚገባና ፈረሱን ለማስዋብ የተለያዩ ማስጌጫዎችን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህም የፈረሰኛ ትጥቅ የሆኑ ኮርቻ፣ ግላስ፣ ልጓም፣ ገንባሌ፣ ሳርያን ኮት፣ ጋሻ ፣ ዘንግና አለንጋ የመሳሰሉትን ማዘጋጀትም ያስፈልጋል።

ሸምጥ ጋላቢዎችና ተወዳዳሪ ፈረሰኞች ፈረሶቻቸውን በሳምንት ሁለት ጊዜ ያሰለጥናሉ። የፈረሶችን ጠንነት ማረጋገጥና መንከባከብ እንዲሁም ንፀህናቸውን መጠበቅና ጉልበት ሰጭ ምግቦችን ለፈረሶቻቸው መመገብ ከዝግጅቶቹ የሚጠቀሱ ናቸው።

በዚህ ሁሉ ወስጥ የማህበሩ ዓላማን በማንገብ አባት ጀግና አርበኞች የከፈሉትን መስዋዕትነትና ተጋድሎን መዘከር እና የፈረስ ውለታን ማሰብ ዋናው አጀንዳቸው ነው።

ፈረስ ለአዊ ህዝብ ሁለገብ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን በአከባቢው በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በባህላዊ እና በሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ውስጥ ፈረስ የሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑም ይጠቀሳል።

የታመሙትን ወደ ሕክምና በማድረስ፣ ተጋቢ ሙሽሮች እና አጃቢዎችን በማጓጓዝ፣ ክብረ በዓላትን በማድመቅ እንዲሁም በሐዘን ጊዜ ሙሾ በማጀብ የማይተካ አገልግሎት ይሰጣል።

ሌላው በአዊ ብሔረሰብ ዘንድ የፈረስ አገልግሎቶችን ለየት የሚያደርገው በግብርናው ዘርፍ የሚያደርገው አበርክቶ ነው። ለሰዎች ትራንስፖርት አገልግሎትና ጭነትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ከማድረስ ባሻገር በሬን ተክቶ የእርሻ አገልግሎት ይሰጣል። በእርሻ ማሣ ላይ ይውላል ከአጨዳ በኋላም እህል የመውቃት ተግባር ያከናውናል።

እነዚህን ዘርፈ ብዙ የፈረስ አገልግሎትና የጥንት አባት ጀግና አርበኛ ፈረሰኞችን ገድል ለማስታወስ ነበር ከ84 ዓመት በፊት “የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር” የተቋቋመው።

ማህበሩ በኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ሀገራዊ ቅርስ ሆኖ በ2014 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወሳል።

ክብረ በዓሉን የቱርዝም መዳረሻ ለማድረግ እና በተባበሩት መንግስታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ለማስዝገብ ጥረት አየተደረገም ይገኛል። ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ