ከወጪ ንግድ ምርቶች ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ሚያዚያ 3/2016 (አዲስ ዋልታ) በበጀት ዓመቱ በ8 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ምርቶች 617 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ገቢው የተገኘው የንግድና ቀጣናዊ ትሰስር ሚኒስቴር ክትትል ከሚያደርግባቸው የወጪ ንግድ ምርቶች መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በስምንት ወሩ ከዘርፉ ወጪ ንግድ 705 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የእቅዱን 87 በመቶ አፈፃጸም መመዝገቡን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታለል፡፡

ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት አፈፃጸም ጋር ሲነፃጸር የ80 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ነው የተገለጸው፡፡

የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ከፍተኛውን ገቢ ያስገኙ ምርቶች መሆኑንም ጠቅሷል ሚኒስተሩ፡፡

የውልና ኢንቨስትመንት እርሻ መመሪያ ተግባራዊ መደረጉ፣ የአኩሪ አተር፣ቀይ ቦሎቄና ማሾ ምርቶች ዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት መሻሻሉና የሰሊጥ ምርት መጨመር በዘርፉ ለተገኘው ውጤት ማደግ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡