በሳሙኤል ሙሉጌታ
ታኅሣሥ 24/2015 (ዋልታ) ለ5 ዓመታት በመማሪያ ክፍል ውስጥ ቆሞ ከመማር፤በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተንበርክኮ እስከማንበብ የደረሰ ለትምህርት የተከፈለ መሰዋትነት፡፡
በበርካታ ውጣ ውረድ እና በተስፋ አስቆራጭ አጋጣሚዎች የተሞላ የተማሪ ግርማ ታሪክ በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ ፍፃሜው አምሮለት 37 ኤ ፕላስ ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ተሻላሚ በመሆን ተመርቋል፡፡
የማይታመን ነገር ግን የሆነ የትምሀርት ዋጋን ልክ ያሳየ ይህ የተማሪ ግርማ ዳባ ይህወት ነው፡፡ወጣቶች ምንም ያህል ፈተና ቢገጥማቸው ፈተናውን አሸንፈው ውጣውረዱን ተሸግረው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ የወጣት ግርማ ታሪክ የውሃ ልክ ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ከኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ሙሎ እስከ ወላይታ ሶዶ የዘለቀው የወጣቱ ህይወት በጋሬጣ የተሞላ ቢሆንም ተማሪው አንድም ቀን ተስፋ ቆርጦ አያውቅም፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር የቀን ሥራ ሰርቷል በጥበቃ ሥራላይም ተሰማርቷል ከዚህ ሁሉ ውጣውረድ በኃላ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን አልፎ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ገባ፡፡
በትምህረት ላይ የሚገጥመው ፈተና ግን በዩኒቨረስቲም ተከተለው፤በሁለተኛ ደረጃ ትምሀረት ቤት እያለ የገጠመው የኩላሊት ህመም በዩኒቨርስቲ ውስጥ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሲሆን ግርማ ግን የጽናት ሰው ነውና ጥርሱን ነክሶ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ፡፡
እየከፋ የመጣው የኩላሊት ህመሙ ግን በክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ትምህርቱን ከመከታተል፤በቤተ መጻሕፍት ለማንበብ ከፍተኛ ጫና አሳደረበት፡፡
የሚወደውን ትምሀርቱ ላለማቋረጥ ግርማ ተስፋ ሳይቆርጥ ያለውን አቅም አሟጦ ትምሀርቱን ለማስቀጠል ወሰነ፡፡
ቆሞ ለመማር ተንበርክኮ ለማንበብ መወሰን
ተማሪ ግርማ ወደ ዲፓርትመንት ኃላፊዎች እና ወደ አስተማሪዎቹ ዘንድ በመሄድ አንድ ሀሳብ አቀረበ ‘’ትምህርቴን እንዳላቋርጥ ቆሜ ክፍል ውስጥ እንድማር ፍቀዱልኝ ‘’አላቸው፤የዲፓርትመንቱ ኃላፊዎችም ለአፍታ ሳያመነቱ ተማሪ ግርማ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ቆሞ እንዲማር ፈቀዱለት፡፡
በዲፓርትመንቱ ኃላፊዎች እና መምህራኑ ቀና ትብብር ትምህርቱን የቀጠለው ግርማ በመማሪያ ክፍል ውስጥ እየቆመ አንዳንዴም በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተንበርክኮ እያነበበ ለሁለት ዓመታት ዘለቀ፡፡
የዲፓርትመንቱ ኃላፊዎች እና ምምህራን አዳዲስ መምህራን ሲመጡ ተማሪ ግርማ በክፍል ውስጥ ቆሞ እንደሚማር አስቀድሞ ግንዝቤ እንደሚያስጨብጡ ወጣት ግርማ ይናገራል፡፡
“በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተንበርክኬ ሳነብ የተማሪዎች ትኩረት በእኔ ላይ በመሆኑ በቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ማንበብ አቆምኩ” የሚለው ግርማ ትምህርቱን ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን በላቀ ውጤት መመረቅ ህልሙ ነበር፡፡
በሁለት ዓመታት የዩኒቨርስቲ ቆይታው የገጠመው ህመም ሳይበግረው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ለቀጣይ የሶስተኛ ዓመት ትምሀርቱ መዘጋጀት ቀጠለ፡፡
ግርማ ትምህርቱን አቋርጦ አልጋ ላይ ዋለ
ሶስተኛ ዓመት ላይ ግን ግርማ በጣም እየከፋ በመጣው የኩላሊት ህመሙ ላይ ተጨማሪ የልብ ህመምን በማስከተል አላጋ ላይ ጣሉት፤ይሄኔ ፅናቱን የሚያውቁት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች ክፉኛ አዘኑ፤ የግርማን ህይወት ለማትረፍም በላቸው አቅም ሁሉ ተረባረቡ፡፡
በወቅቱ የግርማ ትልቁ ችግር የነበረው የመታከሚያ ገንዘብ ሲሆን የገንዘብ ችግሩን ለመፍታት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መምህራን እና የትውልድ ስፍራው ነዋሪዎች ያለቸውን በማዋጣት 80ሺህ ብር ሰብስበው ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ላኩት፡፡
ግርማ ተስፋ አልቆረጠም ጤንነቱ ተሻሽሎ አንድ ቀን ወደ ትምህርት እንደሚመለስ ተስፋ ሰንቆ የነበረ ሲሆን ፡ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማምራት ህክምናውን ሲከታተል ከቆየ በኃላ፤ወደ አንድ የግል ሆስፒታል በማምራት በተደረገለት የጨረር ህክማና ጤንነቱ ተሻሽሎ ከአንድ ዓመት በኃላ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተመለሰ፡፡
በወቅቱ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ትምሀርቴን አቋርጬ ስወጣ የሁሉም ትኩረት የነበረው የኔን ህይወት በማትረፍ ላይ ነበር የሚለው ግርማ በፍጥነት ጤንነቴ ተሻሽሎ ወደ ትምህረት መመለሴ በርካቶችን አስገርሟል ይላል፡፡
ግርማ ከአንድ ዓመት በኃላ ወደ መደበኛ ትምህርቱ ቢመለስም በመማሪያ ክፍል ውስጥ እና በቤተ መጻሕፍት ቆሞ ትምህርት መከታተል እና ማንበቡ የቀጠለ ሲሆን አንዳንዴም ተንበርክኮ ለማንበብ ይገደድ ነበር፡፡
የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ተግቶ የሚሰራው ግርማ ችግር ሳይበግረው ይህንኑ ህልሙንም በመጨረሻ ቆሞ እየተማረ ተንበርክኮ እያጠና ሲብስበት እየተንፏቀቀ 37 ኤ ፕላስ በማምጣት በመጨረሻ የፍርማሲ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡
“በሀገሬው ህዝብ የሚዘወተሩ ባህላዊ መዳኒቶችን ወደ ሳይንሳዊ ህክምና በማምጣት ያስተማረኝን ኅብረተሰብ መርዳት የወደፊት ህልሜ ነው ” የሚለው ወጣት ግርማ ከምረቃ በኃላ የሁለተኛ ምዕራፍ የህይወት ፈተናን ለመጋፈጥ እየተሰናዳ ነው፡፡