ከፖለቲካ አመለካከት ሀገርን ያስቀደመው የሚኒስትሮች ም/ቤት አወቃቀር

መስከረም 26/ 2014 (ዋልታ) አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀር ከፖለቲካ አመለካከት በላይ አገር መቅደም እንዳለበት በተግባር ያሳየ መሆኑን ተሿሚ ሚኒስትሮች ገለጹ።
ሚኒስትሮቹ ሌብነትን በመታገል ዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አብዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት የመንግስታቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ሹመት አጽድቀዋል።
22 ሚኒስትሮችን የያዘው አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አደረጃጀት ከብልጽግና ፓርቲ ባለፈ ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላትን አካትቷል።
ተሿሚ ሚኒስትሮችም እንዲህ ዓይነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አደረጃጀት “የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማሳደግ ከፖለቲካ ልዩነት ይልቅ አገር ማስቀደምን ያስተማረ ነው” ብለዋል።
ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሻለ አገር ለመገንባት አልመው የተመሰረቱ መሆናቸውን አመልክተው፤ በአገር ጉዳይ ላይ ተቀራርበው መስራታቸው ዓላማቸውን በቀላሉ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖለቲካ ልዩነቱን ወደ ኋላ ጥሎ አገርን ከችግር ለማውጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል።
እንደ ሚኒስትሮቹ ገለጻ ሀገርን በማልማት ወደ ብልጽግ ማሻገር የሚቻለው ከታችኛው የመንግስት አደረጃጀት ጀምሮ ግልጽ አሰራሮች በመፍጠርና ሌብነት ሲጠፋ ብቻ ነው።
ዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑና በድህነት ውስጥ እንዲማቅቁ የሚያደርገውም “ሌብነት ነው” ሲሉ ለኢዜአ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአዲሱ የመንግስት መዋቅር የጣለውን እምነት በታማኝነት በቅንነት ለመፈጸም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላቱ ያላቸውን ቁርጠኝነትን አረጋግጠዋል።