ከ129 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) ከ129 ሚሊየን 152 ሺሕ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል 102 ነጥብ 8 ሚሊየን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 26 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ አማካኝነት መያዙን ነው ያስታወቀው፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ አዲስ አበባ ኤር ፖርት እና አዲስ አበባ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 37 ነጥብ 9 ሚሊየን፣ 16 ነጥብ 7 ሚሊየን እና 14 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዛቸው ተመላክቷል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW