ከ29 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – ከግንቦት 13 እስከ 19/2013 ዓ.ም ድረስ ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በሁሉም የጉምሩክ ኬላና መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ባለፈው ሳምንት በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር 27 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ገልጿል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ሀዋሳ፣ ጅግጅጋ እና ሞያሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል ነው የተባለው።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የምግብ ዘይት፣ የጦር መሳሪያዎችና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በፍተሻ፣ በበረራ እና በጥቆማ የተያዙ ሲሆኑ፣ ዕቃዎቹን ሲያጓጉዙ የተገኙ 33 ተሽከርካሪዎች ከዕቃዎቹ ጋር መያዛቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌደራል የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርቧል፡፡