ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች።

በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡሩኒ ሮድሪጌዝ ፓሪላ  ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ዋና ዳይሬክተርነት የአፍሪካ ሕብረት ዶክተር አርከበ እቁበይን በእጩነት ማቅረቡን በተመለከተ እና በቀጣናዊና የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።

አምባሳደሩ ሽብሩ ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ላላት ግንኙነት የላቀ ግምት እንደምትሰጥ እና የሁለቱን አገራት ዘርፈ-ብዙ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በዚህም በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዶክተር አርከበ እቁባይ ለተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጄኔራል ዳይሬክተርንት በዕጩነት ማቅረቧንና መጨረሻ ሦስት ዕጩዎች ውስጥ መካተታቸውን በአፍሪካ ህብረት በኩል ሙሉ ድጋፍ የተሰጣቸውን የአፍሪካ ብቸኛ ተወዳዳሪ መሆናቸውን አምባሳደርሩ  ገልጸዋል፡፡

ዶክተር አርከበ ካለቸው ብቃት እና ድርጅቱን ለመምራት ካስቀመጡት ሪዕይ አንጻር  ቢመረጡ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ላሉ አገራት ጠቃሚ መሆኑን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል።

አምባሳደሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ከግብጽና ሱዳን ጋር ያሉትን ልዩነቶች በውይይትና በድርድር ለመፍታትና ሁሉንም ወገን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ስምምነት እንዲደርስ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ገልፀዉ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ መፍትሄ የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲፈጠር  እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ስለ ኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ በቅርቡ ስለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ እና መንግስት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የህግ የበላይነት የማስከበር እርምጃ በተመለከተም ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት የሚያካሂደውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተቀራርበው ለመስራት መንግስታቸው ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ያቀረበቻቸውን እጩ ኩባ በአዎንታዊ መልኩ ወስዳ እንደሚያዩት ጠቅሰው፣ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ማሳደግ እንደምትፈልግም ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ ለመፍታት እያደረገች ያለው ተግባር ኩባ እንደምትደግፈውና እውቅና እንደምትሰጠው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።