ክልሉ ከ1 ቢሊየን 33 ሚሊየን በላይ ችግኞች ማዘጋጀቱን ገለጸ

የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር
ሚያዝያ 20/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ከ1 ቢሊየን 33 ሚሊየን በላይ ችግኞች ዝግጁ መሆናቸውን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
በቢሮው የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ኃ/ማሪያም በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር 1 ነጥብ 57 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸው፣ አሁን ላይ ከ1 ቢሊየን 33 ሚሊየን በላይ ችግኞች ዝግጁ መሆናቸውን ለዋልታ ተናግረዋል፡፡
የደን፣ ጥምር ደን፣ ፍራፍሬ፣ ቀርከሃ እና የመኖ ተክሎች ከተዘጋጁ ችግኞች መካከል እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
በችግኞች ዝግጅት ዙሪያ መዘግየቶች ቢኖሩም ዕቅዱን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በመኸርና በልግ ወቅቶች ችግኞች የመትከል ስራ እንደሚከናወን የተናገሩት አቶ መንግስቱ፣ ወቅቶችን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን በማቀድ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የችግኝ ተከላ መርኃግብርን ለማሳካት የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ህብረተሰቡን በማንቃት ጉድጓድ የመቆፈር እና ቦታዎችን የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡም ችግኝ መትከል ያለውን ዘርፈብዙ ጠቀሜታ በመረዳት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት ክልሉ ከሚያዘጋጃቸው ችግኞች ውስጥ 25 ሚሊየን ያህሉን ለጎረቤት ሀገራት ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብሮች በክልሉ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና ከነዚህም 84 ነጥብ 5 በመቶ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች የደረሱበትንና ያሉበትን ደረጃ የሚከታተል የማኔጅመንት ቡድን ተቋቁሞ ድጋፍና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑም ገልጸዋል፡፡
(በአድማሱ አራጋው)
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችን
https://www.facebook.com/waltainfo
የአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የትዊተር ገፃችን
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!