ግንቦት 07/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል መጀመሩ ተገለጸ፡፡
በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አንተነህ ፍቃዱ፣ አረንጓዴ አሻራ ሥራ ለአካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አቶ አንተነህ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት ለኑሮ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ሀገራችን ለአየር መዛባት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ትንሽ ቢሆንም የችግሩ ሰለባ መሆኗ ስለማይቀር ለዘርፉ ኢኮኖሚ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
አክለውም በሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል የተፋሰስ ልማት ስራ በዋናነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለምግብ፣ ለመኖ፣ ለማገዶ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ሚሆኑ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ኃላፊው አሳስበዋል፡፡
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድርያስ ጌታ በዞኑ ከዚህ በፊት በተሰሩ የችግኝ ተከላ ሥራዎች ብዙ አዎንታዊ ለውጦች መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ስራ ሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ችግኝ በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያደረገ ትልቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ ዘንድሮ 18 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱንና ሀገራችን ለአጎራባች ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ካቀደችው አንድ ቢሊዮን ችግኝ የዞኑ ድርሻ የሆነውን 10 ሚሊዮን ችግኞችን ለማበርከት ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ነው ዶክተር እንድርያስ የገለጹት፡፡
የወላይታ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ጴጥሮስ ኃይለማሪያም አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራን ከስነ ህይወታዊ ሥራ ጋር አያይዞ በመስራት የሚጠበቀውን ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችል በቂ እርጥበት ባለበት ወቅት ችግኝ ተከላ የማካሄድ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም ከዚህ በፊት በተሰሩ ችግኝ ተከላ ሥራዎች ከመቶ 11 የነበረው የደን ሽፋን በአሁኑ ጊዜ ወደ 23 ከመቶ ማደግ መቻሉንና ከዚህ ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት እተስተካከለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚካሄደው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሁሉም መዋቅሮች በተሻለ ሁኔታ ተጀምሮ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት አቶ ጴጥሮስ የተጀመረውን አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተግባርን ስኬታማ ለማድረግ መላው ህብረተሰብ አዳዲስ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በተጀመረው ህብረተሰብ አቀፍ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ከዞን ፣ ከክልልና ከፌድራል የመጡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን፣ የዞኑ ተወላጆች፣ የዞንና የወረዳ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውን ከወላይታ ዞን መንግስት ኮሚዩኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡