ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከ25 ሺሕ በላይ ተመልካቾችን በሚይዝ ስታዲዬም ከደጋፊዎች ጋር ትውውቅ ያደርጋል

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

ታኅሣሥ 25/2015 (ዋልታ) ለሳኡዲ አረቢያ አልናስር ከለብ ለመጫወት የፈረመው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከ25 ሺሕ በላይ ተመልካቾችን በሚይዝ ስታዲዬም ከደጋፊዎች ጋር ትውውቅ ያደርጋል፡፡

የፖርቹጋሉ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከደጋፊዎች ጋር ትውውቅ ለማድርግም ሪያድ ገብቷል፡፡
የክለቡ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሮናልዶ በዛሬው ዕለት ከ25 ሺሕ በላይ ተመልካቾችን በሚይዝ ስታዲዬም ከደጋፊዋች ጋር ትውውቅ ያደርጋል፡፡

የ5 ጊዜ ሻምፒዮንስ ሊግ እና 7 ጊዜ የሊግ ዋንጫዎች አሸናፊው ሮናልዶ ወደ አልናስር መዛወሩን ተከትሎ ክለቡ በሰዓታት ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያቸውን የተቀላቀሉ ሲሆን ባሁኑ ሰዓት 7.4 ሚሊዮን የኢንስታግራም ተከታዮችን አፍርተዋል፡፡

ሮናልዶ 7 ቁጥር ማለያን የሚለብስ ሲሆን በክለቡ እስከ ሰኔ 2025 ለመቆየትም ተስማምቷል፡፡

ተጨዋቹ ርያድ ሲገባ የራሱን የግል አሰልጣኝ ቡድንና የጸጥታ ጥበቃ ድርጅት አስከትሎ መሆኑን የአልጄዚራ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ተጨዋቹ ለፒርስ ሞርጋን ከሰጠው አነጋጋሪ ቃለ መጠይቅ በኋላ ከቀድሞው ክለቡ ማንችስተር ዩናይትድ ጋር መለያየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ከዓለም ዋንጫ መልስ በሪያል ማድሪድ ልምምድ ሲያደርግ የነበረው ሮናልዶ ባሳለፍነው ሳምንት በ213 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደመወዝ ወደ አል ናስር ለመዘዋወር ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡