ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

ግንቦት 11/2015 (ዋልታ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ አራት ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር በመሄድ ለሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዚህም በጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ ሀረሪ፣ ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ላይ የተሳታፊዎች ልየታው እንደሚጀመር አንስተዋል፡፡

ከወረዳ እስከ ዞን ከተሞች በሚደረገው ልየታ የተመረጡ ተሳታፊዎችም ወደ ክልሉ በመሄድ ተወካዮቻቸውን እንደሚመርጡም ተነስቷል።

ሂደቱን የመታዘብ ሚና እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ተባባሪ ተቋማት ስለመመረጣቸው የተነሳ ሲሆን 11ዱም ኮሚሽነሮች ወደየአካባቢዎቹ በመሄድ የልየታ ስራውን እንደሚከታተሉ ተገልጿል፡፡

ተወካዮች ከተለዩ በኋላ የመወያያ አጀንዳ የማሰባሰቡ ስራ እንደሚቀጥል የተነሳ ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአጀንዳ የማሰባሰቡ ስራ እንደሚሳተፍም ተጠቁሟል፡፡

በትዕግስት ዘላለም