ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን ለማዘመን ስምምነት ተፈራረመ

ኅዳር 15/2015 (ዋልታ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሕንጻን ለማደስና ለማዘመን የሚያስችለውን ስምምነት ፈረመ፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር መሰረት ዳምጤ ናቸው፡፡

ባለ 10 ወለሉን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሕንጻ የማደስና የማዘመን ሥራው በሁለት ምዕራፎች የሚከናወን ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር የእድሳት ሥራ በሥድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በአጠቃላይ ሥራውን ለማከናወን ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ 269 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መመደቡ ተመላክቷል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሕንጻን የእድሳት ሥራ፣ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶችን ጨምሮ ሙሉ ዲዛይን እና የግንባታ ሥራ እንደሚያከናውንም የቤቶች ኮርፖሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

የቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል “የእድሳት እና የማዘመን ሥራውን በተያዘለት በጀት፣ የጥራት ደረጃ እና ጊዜ አጠናቀን እናስረክባለን” ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው “ኮርፖሬሽኑ ለጥራትና ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ስላረጋገጥን የሥራ ስምምነት አድርገናል” ነው ያሉት።

ሥራውን ኮርፖሬሽኑ በአጭር ጊዜ እና በውሉ መሰረት አጠናቆ እንደሚያስረክብ ያላቸውን እምነት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ለጥራት እና ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ በተግባር ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW