ኳታር በዓለም ዋንጫ ለመታደም ወደ ሀገሪቱ የሚያመሩ ደጋፊዎችን በተመለከተ ጠንከር ያለ ሕግ ደነገገች

መስከረም 24/2014 (ዋልታ) የ2022ቱን የዓለም ዋንጫ የምታስተናግደው ኳታር የዓለም ዋንጫውን በስቴዲየሞች ተገኝተው በሚታደሙ ደጋፊዎች ላይ ጠንከር ያለ ሕግ ደንግጋለች፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ውድድር የሆነው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሊጀመር ከ50 ቀናት በታች ቀርተውታል፡፡

በዚህ የዓለም ዋንጫ ውድድር የኳታር እግር ኳስ ፌደሬሽን ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ እንዲሁም ከእስር እስከሞት ቅጣት የሚያደርሱ ሕጎችና ደንቦችን በተለይ በደጋፊዎች ላይ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በኳታር ከ21 ዓመት በላይ የሆነ ሰው አልኮል መጠጣት ይፈቀድለታል የሚል ሕግ እንዳለ ቢነገርም የአለም ዋነጫውን ለመከታተል ወደሀገሪቱ የሚገባ ማነኛውም ደጋፊ ጨዋታዎች በሚደረጉበት ስፍራ እና ሰዓት የአልኮል መጠጥ መግዛትና መጠቀም አይፈቀድለትም፡፡

አልኮል መጠጣት የሚፈልግ ደጋፊ፤ በተከለለ ስፍራ፣ እና በተወሰነ የሰዓት ገደብ ውስጥ መጠቀም እንደሚችልም ሕጉ ይደነግጋል፡፡

ይህንን ሕግ ተላልፎ መገኘት እና በተለይ ደግሞ አደንዛዥ እጾችን መጠቀም ከበድ ላለ ቅጣት እንደሚዳርግም ተገልጿል፡፡

አለባበስን በተመለከተም በተለይ ለሴቶች ትከሻቸውን የሚያሳይ እና አጫጭር ቀሚሶች መልበስ የተከለከለ ሲሆን ይንን ሕግ ተላልፎ መገኘት ለእስር ሊዳርግ ይችላል፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በግልጽ መሳሳም ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን በተለይ ደግሞ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እስከሞት ለሚያደርስ ቅጣት እንደሚዳርግ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

በነስረዲን ኑሩ