ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

መጋቢት 02/2013 (ዋልታ) -የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ መለሰ አለሙ በወቅታዊ ሀገራዊ እና ከተማ አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ወይይት አካሂደዋል።
ኪነጥበብ ሀገርን በመገንባት፣ ዜጋን ለመቅረጽ፣ ሰላም እና አንድነትን በማጠናከር እንዲሁም ህዝብን ለልማት በማነሳሳት ትልቁ መሣሪያ ነው ሲሉ ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡
የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፤ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረውም በሙያቸው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ወ/ሮ አዳነች ጠቁመዋል፡፡
የከተማዋን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲያሳኩ የታየው የሰላም እና ሀገራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሙያቸው እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ወ/ሮ አዳነች አሳስበዋል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ የተጫወቱት ሚና የላቀ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በሙያቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተለይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህግ ማስከበር ዘመቻ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲደረጉ ህብረተሰቡን በማነሳሳት ያደረጉት ተሳትፎ አጅግ የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኪነጥበብ ዘርፉን ማዕከል ያደረጉት መሆናቸውን የገለፁት ወ/ሮ አዳነች የአድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎሜትር ሙዚየም እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የባህል እና የኪነጥበብ ማንጸባረቂያ ናቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ የኪነጥበብ ዘርፉ እንዲጠናከር በእቅድ እና በፓሊሲ እንዲደገፍ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ከውይይቱ በኃላም የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ የኪነጥበብ ማህበራት ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።