ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሁሉም ነገር መሠረት የሆነውን ሠላምን በጽኑ መሠረት በማጽናት ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።

በዚህም ሀገራችን መልካቸውን እየቀያዬሩ ከውስጥና ከውጪ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በመቀልበስ አስደማሚ ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለለች።

በብልጽግና ጉዞዋ ስጋት የገባቸው ሃይሎች ሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተከሰቱት የጸጥታ ችግሮች አልበቃ ብሏት ዛሬም የጥፋት አጀንዳቸውን ዘርግተው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስም አልፎ አልፎ የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን መከላከያ ሠራዊትን በመተንኮስ ሀገራችን ከጀመረችው ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ ዓላማ ያለው መሆኑ ግልጽ ነው።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የአንድነታችን አርማ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ በመቀልበስ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ በአስተማማኝ ሁኔታ መቀጠል ይጠበቅብናል።

በምንም ሁኔታ የሀገር መከላከያን ሠራዊትን መንካት የሀገርን ሉዓላዊነት መንካት በመሆኑ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት እና ሕዝብ ሁሌም የአንድነታችን አርማ ከሆነው ጀግናው የሀገር መከላከያ ጎን መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

ይህንን ለሀገሩ ፍቅር ብቻ የሚዋደቅ እና ኢትዮጵያን አጽንቶ ከነክብሯ ለማስቀጠል መስዋዕትነት ለሚከፍለው ሠራዊት ያለን ክብርም የላቀ ነው።

ሀገራዊ አንድነትን በጽኑ መሠረት ላይ እየገመድን በምንገኝበት በዚህ ወቅት አንዱ ያለሌላው ምንም በመሆኑ፣ የሀገራችን ሕዝቦች መብቶችና ጥቅሞች አንዱ ከሌለኛው ጥቅሞች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በጥልቀት መገንዘብ ይገባል።

በአሁኗ ኢትዮጵያ የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ሀገርንና ሕዝብን ያስቀደመ ሠላማዊ ምክክር እንጂ በትጥቅ ትግል የሚመለስ ጥያቄ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፤ ተቀባይነትም የለውም።

መንግስት በተለይም ከለውጡ ወዲህ ማንኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፈታት ሁሌም ዝግጁ ከመሆን አልፎ፣ ባለፉት ጊዜያት ይህንን ለሠላም ያለውን ጽኑ እምነት በተግባር አረጋግጧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጃውሳው እየተስተዋለ ያለው የኃይል እንቅስቃሴ የክልሉን ሕዝብ ለማሰቃየት የተፈጠረ ኃይል እንጂ የአማራ ክልል ሕዝብ ወኪል አለመሆኑን መገንዘብ ይጠበቃል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተለይም ደግሞ የአማራ ክልል ሕዝብ የአንድነታችን አርማ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም፣ አሁን በክልሉ የገጠመውን ፈተና በመቀልበስ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ በአስተማማኝ ሁኔታ መቀጠል ይጠበቅብናል።

የአማራ ብሔራዊ ክልል ቀደም ሲል በነበረው ጦርነት ከደረሰበት ሁለንተናዊ ጉዳት በአግባቡ ሳይወጣ ጃውሳው በክልሉ እየፈጠረ ያለውን ፈተና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በጽኑ ያወግዛል።

በመሆኑም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትና ሕዝብ ከፌዴራል መንግስትና ከአማራ ክልል ሕዝብ ጎን በመቆም ይሄንን ሀገር አፍራሽ ኃይል ለመታገል ያለውን ዝግጁነት ያረጋገጣል።

በመጨረሻም በአማራ ክልል መንግስት እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉ ወደ ቀደመው ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንደሚመለስ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ያለውን ሙሉ እምነት ይገልጻል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም
አሶሳ፣