ወደ አዲስ አበባ እየገባ ያለው ምርት ለታለመለት አላማና ለታሰበለት ህዝብ መዋል አለበት- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – ወደ ከተማ እየገባ ያለው ምርት ለታለመለት አላማ እና ለታሰበለት ህዝብ መዋል እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ፡፡

ሕብረተሰቡ በአቅራብያው ባሉ የሸማች ማህበራት ሄዶ በመሸመት እና በተለያዩ መንገዶች ነዋሪውን የሚያጉላሉትን ነጋዴዎችን በማጋለጥ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ነው ያሳሰቡት፡፡

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሸማቾች ማህበራት ጋር እየታየ ያለውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ በተሰሩ ስራዎች ላይ ውጤት ማየት መቻሉን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፣ የእህል ምርት በይበልጥ ጤፍ በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ የተሰራው ስራ የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር እንዲሁም አቅርቦት በመጨመር የገበያ መረጋጋትን ለማየት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፋቸው፣ የህብረት ስራ ዩኒየኖችን እና የሸማቾች ማህበራትንም የተሰጣቸውን ገንዘብ በቀጥታ እና በታማኝነት ለተባለው አላማ በማዋል ለተጫወቱት አዎንታዊ ሚና ምስጋና አቅርበዋል፡፡